The Constitutionality of Proc.97/98


Guest2024/02/24 16:00
Follow

የአዋጅ ቁጥር 97/90 ሕገ- መንግስታዊ ቅቡልነት

ብርሐኑ በየነ ብርሐኑ (LL.M, LL.B)

 Email -  [email protected][email protected]

 

1.   መግቢያ

አዋጅ ቁ.97/90[1] ባንኮች ብድር ሲሰጡ የመያዣ መብት ያቋቋሙበትን ንብረት የፍ/ቤት ይሁንታ ሳያስፈልጋቸው በራሳቸው ለመሸጥ እና ከሽያጩ የተገኘውን ገንዘብ ለብድሩ መክፈያነት ለማዋል እንዲችሉ ሥርዐት የዘረጋ አዋጅ ነው፡፡አዋጁ ባንኮች ሽያጩን ለማከናወን መከተል ያለባቸውን ዝርዝር የአፈጻጸም ሥነ-ሥርዐቶችን[2] የያዘ ሲሆን  ባንኮች ከፍ/ቤት ውጭ መያዣ ሊሸጡ የሚችሉት በማናቸውም ሁኔታ ሳይሆን ብድሩ ሳይከፈል ሲቀር ሽያጩን እንዲያደርጉ ከተበዳሪዎች/አስያዦች  ጋር ቀድሞ በተደረገ ስምምነት መብት ከተሰጣቸው ብቻ መሆኑን ይደነግጋል[3]፡፡

 

የአዋጁ ዐላማ በአጭሩ ባንኮች ብድር ለማስመለስ ወደፍ/ቤት ቢሄዱ ከሚወስድባቸው ጊዜ ባጠረ እና ከሚያስወጣው ወጪ ባነሰ መልኩ የሰጡትን ብድር መሰብሰብ እንዲችሉ አስቻይ ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ ባንኮች ከህዝብ በአደራ መልክ የሰበሰቡትን ገንዘብ ስለሆነ የሚያበድሩት የሰጡት ብድር በተቀላጠፈ ሁኔታ የሚመለስበት ሥርዐት ካልኖረ የህዝቡ ገንዘብ ለአደጋ ይጋለጣል፣የባንኮች ህልውናም ሊያከትም ይችላል፡፡ ባንኮች በተፈጥሯቸው ለሥርዐት-ውድቀት-አደጋ(systemic risk) የተጋለጡ በመሆናቸው፣ የባንኮች ህልውና አደጋ ውስጥ ሲወድቅ  አጠቃላይ  ኢኮኖሚውም አደጋ ውስጥ ይወድቃል፡፡ በመሆኑም፣የባንኮችን ጤንነት በመጠበቅ ኢኮኖሚው ላይ ያላቸውን  ሚና ለማስቀጠል ከፍተኛ ሚና ከሚጫወቱት ነገሮች ውስጥ አዋጅ ቁ. 97/90 አንዱ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡በሌላ አባባል፣ ይህ አዋጅ መጠን -ሰፊ የህዝብ ጥቅምን (public interest) የሚያስጠብቅ አዋጅ ነው፡፡

 

የአዋጁ ተጽኖ በብድር አሰባሰብ ላይ ብቻ  የተወሰነ አይደለም የብድር አሰጣጥ ላይም ከፍተኛ ተጽኖ አለው፡፡ አዋጁ የብድር አመላለስን ፈጣን እና ቀልጣፋ በማድረጉ እና የባንኮችን የሰጠሁት ብድር ላይመለስ ይችላል የሚለውን ስጋት በመቀረፉ፣መያዣ ለሚያቀርቡ ተበዳሪዎች ባንኮች በአጭር ጊዜ ውስጥ በአነስተኛ ወጪ የብድር አገልገሎት እንዲሰጡ ስላደረጋቸው ህጉ ለባንኮች ብቻ ሳይሆን ለተበዳሪዎችም ጠቃሚ ነው፡፡

 

አዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት 26 ዐመት ያስገኘውን ጥቅም ስንመለከት ባንኮችን ከመፍረስ ታድጓል፣ የተበላሹ ብድሮች ምጣኔ ከ50% ወደ ከ5% በታች እንዲሆን አድርጓል፣ ባንኮች የአስቀማጮችን አመኔታ አግኝተው የቁጠባ ባህል እንዲዳብር አድርጓል፣ በትሪሊየን የሚቁጠር ገንዘብ በብድር መልክ ለተበዳሪዎች  እንዲሰጥ ሁኔታዎችን አመቻችቷል፡፡ በተለይ ደግሞ፣በሀገሪቱ፣ ብድር ለማስመለስ የሚያግዙ ተቋማት (ለምሳሌ credit rating agencies, secondary debt markets ወዘተ) ባለመኖራቸው የተፈጠረውን ክፍተት አሉታዊ ተጽኖዎችን አዋጁ ሊገድብ ችሏል፡፡

 

ባጠቃላይ፣ አዋጁ ከብድር አሰጣጥ እስከ አሰባሰብ ላይ ከፍተኛ አዎንታዊ ተጽኖ በመፍጠር የባንኮች ህልውናን በማስጠበቅ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ሚና ያለው የህዘብ ጥቅም የሚያረጋግጥ አዋጅ ነው፡፡ አዋጁን መሰል ህግ የዳበረ ህገ-መንግስታዊ ሥርዐት ባላቸው ሀገሮች ጭምር የሚገኝ ሲሆን አዋጁም የወጣው የእነርሱን ተሞክሮ በመውሰድ ነው፡፡

 

ባለፉት 26 ዐመታት አዋጁ ተፈጻሚ የሆነው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ሳይሆን ከመላው ህዝብ የተሰበሰበውን ገንዘብ ከባንኮች ላይ ለመበደር የታደሉ  ማለትም በኢኮኖሚ ዐቅማቸው፣ በትምህርት ደረጃቸው፣ በሂወት ልማዳቸው የተሻሉ እና ድምጻቸውን ማሰማት የሚችሉ እና ከባንኮች ጋር ተደራድረው ጥቅማቸውን ያሰጠበቀ የብድር እና የመያዣ ውል ከሚፈርሙ የላይኛው የህብረተሰብ ክፍል ላይ ነው፡፡ ይሁንእንጂ፣አዋጁ የግለሰቦችን ህገ-መንግስታዊ የመበት ጥሰት አስከትሏል እና ኢህገ-መንግስታዊ ነው የሚል አቋም ሲንጸባረቅ ይሰማል፡፡

 

የዚህ ጹሁፍ ዐላማ ከላይ የተገለጸው አቋም  አዋጁን በተዛባ መልክ  በመረዳት የሚቀርብ መሆኑን ለማሳየት እና አዋጁ የህገ-መንግስታዊነት ጉድለት የሌለበት የህዝብ ጥቅምን ከተበዳሪዎች/አስያዦች ህገ-መንግስታዊ መብት ጋር  በማጣጣም የተቀረጸ እና ህገ-መንግስታዊ  ቅቡልነት ያለው መሆኑን ማሳየት ነው፡፡

 

2.  አዋጁ ሕገ መንግስቱ ካስቀመጣቸው ፍትሕ የማግኘት መብት (Right of Access to Justice) እና የንብረት መብት (The Right to property)  ጋር አይጋጭም

መግቢያው ላይ እንደተጠቆመው አዋጁ የወጣው የህዝብን ጥቅም(public interest) ለማስጠበቅ እና ያስጠበቀ ቢሆንም አዋጁ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 37 ላይ ከተደነገገው ፍትሕ የማግኘት መብት (Right of Access to Justice) እና በአንቀፅ 40 ላይ ከተደነገገው የንብረት መብት (Right to property) ጋር ይጋጫል/ይቃረናል የሚል አቋም ሲንጸባረቅ ይስተዋላል፡፡ እንደሚታወቀው ፣ ለህዝብ ጥቅም የወጣ ህግ የግለሰቦች መብት ላይ ተጽኖ ቢኖረው እንኳ ህገ- መንግስታዊ ቅቡልነት አለው፡፡የአዋጁ ቁ. 97/90 የህገ-መንግስታዊ ቅቡልነት የሚያረጋግጠው ግን የህዝብ ጥቅም ለማስከበር የወጣ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን አዋጁ ይህን ሚና የሚጫወተው ከላይ የተጠቀሱትን የሕገ መንግስቱን ድንጋጌዎችንም ሆነ ሌሎች ህገ-መንግስቱ ላይ የተረጋገጡ የግለሰብ መብቶችን ሳይገድብ በመሆኑ ነው፡፡ አጭር ማብራሪያ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

2.1.   አዋጅ ቁ.97/90 ፍትሕ የማግኘት መብት አይነፍግም

አዋጁ በፍ/ቤት የመዳኘትን ወይም ፍትህ የማግኘትን የግለሰቦች መበት ጥሷል የሚል ወቀሳ የሚሰነዘርበት ብድር ሳይከፈል ሲቀር በዋስትናነት የቀረበው የመያዣ ንብረት ያለፍ/ቤት ጣልቃ ገብነት ባንኩ ለመሸጥ ይችላል በሚል በባንኮች እና አስያዦች መካከል የሚደረግ ስምምነት ተፈጻሚ ነው የሚል አንቀጽ አዋጁ በመያዙ ነው(የአዋጁን አንቀጽ 3 ይመለከቷል)፡፡ ይሁንእንጂ፣ ይህ ወቀሳ ሰህተት ነው፡፡አዋጁ በፍ/ቤት የመዳኘትን ወይም ፍትህ የማግኘትን መብት አይጥስም፤ ምክንያቱም፡-

1ኛ) ፈቃድ የሰጠ ግለሰብ ፈቃድ በሰጠበት ሁኔታ በሚፈጸም ድርጊት በህገ-መንግስቱ የተሰጠው መብቱ ተጥሷል ማለት አይቻልም ፣

2ኛ) አዋጁ ፍትህን የሚያረጋግጥ፣የመደመጥ ዕድል የሚሰጥ ሥርዐት ያቀፈ እና ይህ ሥርዐት ካልተከበረ ደግሞ በፍ/ቤት በኩል ዕርምት እንዲወሰድ የደነገገ ነው፡፡

አነዚህ ነጥቦችን አንድ በአንድ እንመልከታቸው፡፡

2.1.1. ፈቃድ የሰጠ ግለሰብ ፈቃድ በሰጠበት ሁኔታ በሚፈጸም ድርጊት በህገ-መንግስቱ የተሰጠው መብቱ ተጥሷል ማለት አይቻልም

በአዋጅ ቁ. 97/90 መሰረት ባንኮች የመያዣ ንብረት ያለፍ/ቤት ጣልቃ ገብነት ለመሸጥ የሚችሉት ይህን ስምምነት መያዣ ሰጭው ግለሰብ ከባንኩ ጋር በሚገባው የመያዣ ውል ላይ ከሰጠ ብቻ ነው(የአዋጁን አንቀጽ 3 ይመለከቷል)፡፡ ይህን ስምምነት ያልሰጠ አስያዥ ከፍ/ቤት ውጪ ለሚካሄድ ሽያጭ የተጋለጠ አይደለም፡፡በመሆኑም፣ስምምነት የሰጠ ግለሰብ በሰጠው ስምምነት መሰረት የተፈጸመን ድርጊት መብቴን ጥሷል የሚልበት አግባብ የለም፡፡

 

እንደሚታወቀው፣ በህገ -መንግስት ላይ የተቀመጡ መብቶች ፍትህ የማግኘትን መብት ጨምሮ ተጣሱ የሚባሉት ያለግለሰቡ ፈቃድ ሲፈጸሙ ነው፡፡ የግል መረጃውን አሳልፎ የሰጠ ሰው የግላዊነት መብቴ(the right to privacy) ተጥሶብኛል የሚልበት አግባብ የለም፡፡ እንዲሁም፣ አለመግባባታቸውን ከፍ/ቤት ውጪ  በአማራጭ የክርክር መፍቻ መንገድ ለመፍታት የተስማሙ ሰዎች ፍ/ቤት ሲቀርቡ ፍ/ቤቶች ጉዳዩን አናስተናግድም በሚሏቸው ጊዜ ፍትህ የማግኘት መብት መንፈግ ተብሎ አይቆጠርም፡፡

በአጠቃላይ፣ አንድ ግለሰቡ በነጻ ፈቃዱ በሰጠው ስምምነት መሰረት የሚፈጸም ድርጊት የመብት ጥሰት አይባልም፡፡ አዋጅ ቁ. 97/90 አስያዡ ንብረቴ ከፍ/ቤት ውጪ በባንክ ይሸጥ ብሎ የሚሰጠው ፈቃድ ተፈጻሚ ነው ማለቱ እና የሚፈጸምነትን መንገድ ማስቀመጡ ከህገ-መንግስቱ ጋር የሚቃረን አያደርገውም፡፡ምክንያቱም፣ህገ-መንግስቱ ላይ ለግለሰቦች የተሰጡ መብቶች በግሰቦች ፈቃድ/ስምምነት ሊተው (waive ሊደረጉ) ይችላሉ፡፡[4] አንድ ጸሀፊ በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲህ ብለዋል፡-

 

"…an individual can normally consent to or waive what would otherwise be a violation of their own constitutional rights."[5]

 

2.1.2. አዋጁ ፍትህ ላይ የሚያደርስ፣የመደመጥ ዕድል የሚሰጥ ሥርዐት ያቀፈ  እና ይህ ሥርዐት ካልተከበረ  ደግሞ በፍ/ቤት በኩል ዕርምት እንዲወሰድ የደነገገ ነው፡

ፍትሕ የማግኘት መብት የሚረጋገጠው/የሚገለፀው ፍ/ቤት በመሄድ ብቻ አይደለም፡፡ ህግ አውጭው በሚያወጣው ህግ ላይ ለግሰቦች መብት ጥበቃ የሚያበጁ ድንጋጌዎች በማስቀመጥም ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ መንግስት ለህዝብ ጥቅም በሚል የግል ንብረቶችን ሲወስድ የፍ/ቤት ጣ/ገብነት ሳይኖር ዝርዝር ድንጋጌዎችን  በመከተል ነው፡፡ ፍ/ቤቶች ጉዳዩ  ውስጥ የሚገቡት ዝርዝር ድንጋጌዎች ሳይከበሩ ሲቀር ነው፡፡ በተመሳሳይ አዋጅ ቁ. 97/90 ባንኮች የመያዣ ንብረት እንዲሸጡ የፈቀደው ስምምነት ሲኖር ብቻ ቢሆንም ስምምነት እስከተገኘ ድረስ በሚል ባንኮች ንብረቱን እንደፈቀዱ እንዲሸጡ አይፈቅድም፡፡ ዝርዝር ሥርዐት አስቀምጧል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ብድሩ እንዳልተከፈለ ይቆጠራል መባል አለበት፡፡በብሄራዊ ባንክ መመሪያ መሰረት ብድሩ አልተከፈልም ማለት የሚቻለው ተበዳሪው መከፈል ካለበት ጊዜ በ90 ቀን ከዘገየ ነው፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ ባንኮች ምንም ዐይነት የሽያጭ ሂደት ከመጀመራቸው በፊት 90 ቀን የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው፡፡

 

ከዚያ በኋላ በአዋጁ አንቀጽ 3 ላይ በተቀመጠው መሰረት የ30 ቀን ማስጠንቀቂያ የመስጠት ግዴታ ባንኮች ላይ ተጥሏል፡፡ ስለዚህ፣ ይህ ሁሉ ጊዜ አስያዦች ንብረታቸው ከመሸጡ በፊት  ከባንኩ ጋር በመነጋገር መፍትሄ እንዲፈልጉ ይረዳቸዋል፡፡ ሁሉም ባንክ "ወርክአውት" የሚባል ክፍል ያላቸው ሲሆን ይህ ክፍል ተበዳሪወች ብድራቸውን ይከፍሉ ዘንድ ከፍተኛ የማስታመም ሥራ ይሰራል፡፡ በሂደቱ ቅሬታ ከተፈጠረ አስያዥ ለባንኮች የበላይ አመራር ቅሬታ ያቀርባል፣ መፍትሄ ከላገኘ  ለብሄራዊ ባንክ ቅሬታ ያቀርባል፡፡ባጠቃላይ የመደመጥ ዕድል ተፈጥሯል፡፡[6]

 

ከላይ በጠቀስናቸው ጊዜዎች የዘረዘርናቸው ድርጊቶች ወደመፍትሄ ካልመሩ ንብረቱ ለሀራጅ ይቀርባል፡፡ የሀራጁ ጠቅላላ ሂደት አሁንም ለባንኮች የተተወ ሳይሆን በፍ/ሥ/ሥ/ህ 394-449 መሰረት ይሆናል( የአዋጁን አንቀጽ 6 ይመለከቷል)፡፡

 

ከላይ የተዘረዘሩትን የተበዳሪዎች/አስያዡች መብት ላይ ጥበቃ ለማደረግ አዋጁ ያስቀመጣቸው ስነ-ሥርዐቶች በአግባቡ ሳይተገበሩ  ሀራጅ ከተካሄደ ወይም  ከመያዣ ውሉ ጋር በተያያዘ ጥያቄ ቢኖር የአዋጁ አንቀጽ 7ን በመጠቀም ወይም/ እና ከአዋጁ አንቀጽ 6 እንደምንረዳው የፍ/ሥ/ሥ/ህ/ 444-447 በመጠቀም  ፍ/ቤት በመቅረብ ባንኮች በመሸጡ ሂደት ጥፋት ካጠፉ የእርምት እርማጃ እንዲወሰድባቸው ማድረግ ይቻላል፡፡ ስለዚህ፣ ይህን ሁሉ ሥርዐት የዘረጋን አዋጅ  ፍትህ የማግኘት መብት ይጥሳል ማለት ፍትህ የማግኘት መብት የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ ካለመረዳት የሚመነጭ ነው፡፡  አዋጁ ፍ/ቤቶች የባንኮች የሽያጭ  ሂደት ላይ ያለገደብ በማናቸውም ምክንያት እና በማንኛውም ሠዐት ላይ ጣልቃ እንዲገቡ አለመፍቀዱ ፍትህ የማግኘት መብት እንደጣሰ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፡፡

  

2.2.   አዋጁ ከአስያዦች የንብረት መብት ጋር አይጋጭም፣የአዋጁን ተፈጻሚነት መገደብ ግን ከአስቀማጮች እና ከባንኮች የንብረት መበት ጋር ይጋጫል

ህገ-መንግስቱ ማንኛውም ሰው ንበረቱን ያለተገቢው ሥርዐት (with out due process) እንዲያጣው ሊደረግ አይባም ሲል ይደነግጋል፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው በአዋጅ ቁ.97/90 ባንኮች የመያዣ ንብረት ያለፍ/ቤት ይሁንታ የሚሸጡት አስያዦች በሰጡት ስምምነት መሰረት፣ብድራቸውን ሳይከፍሉ ሲቀሩ፣ ተበዳሪዎች ብድራቸውን እንዲከፍሉ እና ንበረታቸውን እንዲያድኑ ዕድል ተሰጥቶ፣ይህን ዕድል ካልተጠቀሙ ለህዝብ ክፍት በሆነ ግልጽ ሀራጅ ገበያው በሚያስቀምጠው ዋጋ በመሸጥ እና ይህን ሥርዐት ባለመከትል ሽያጭ ከተከናወነ ለዕርምት ጉዳዩ ወደ ፍ/ቤት የሚወሰድበት ሥርዐት በማስቀመጥ ነው፡፡ ብድር ሳይከፈል ሲቀር የመያዣው ንብረት ቀድሞ የተሰጠ ስምምነት መሰረት በማድረግ በዘፈቀደ ሳይሆን ዝርዝር ሥርዐት ተጠብቆ  የሚሸጥበት ሁኔታ  በተደነገገበት እና ይህ ሥርዐት ሳይጠበቅ ሲሸጥ ደግሞ በፍ/ቤት ሽያጩን የመቃውም[7] እና/ወይም ካሳ የመጠየቅ[8] ሥርዐት በተዘረጋበት ሁኔታ አዋጁ ግለሰቦች ያለተገቢው ሥርዐት (with out due process)  ንብረታቸውን እንዲያጡ ያደርጋል የሚባልበት አግባብ የለም፡፡[9]

 

አዋጅ ቁጥር 97/90 ብድር በፍጥነት እንዲመለስ የሚያደርግ ህግ ነው፡፡አዋጁ ኢህገ-መንግስታዊ ነው በማለት በአዋጁ መሰረት የሚሸጡ የመያዣ ንብረቶች አሻሻጥ  ላይ እና የመያዣ ውሎችን በተመለከተ ፍ/ቤቶች ያለገደብ ጣልቃ የሚገቡ ከሆነ[10] ፣የአዋጁን ዐላማ ሙሉለሙሉ በማጥፋት  በተጓተተ ሥርዐት ብድር ይመለስ እንደማለት ነው፡፡ይህ ሁኔታ ግን የመያዣው ንብረት እንዲጠፋ፣ እንዲወድም በማድረግ ባንኩ የሰጠው ብድር መልሶ እንዳያገኝ ያደርጋል፡፡ ይህ አስቀማጮች ያስቀመጡትን ገንዘብ በፈለጉ ጊዜ ከባንኩ ጠይቀው እንዳያገኙ የሚያደረግ የንብረት መብታቸውን የሚነካ ሲሆን ባንኮች ያበደሩትን ገንዘብ እንዲያጡ ከተደረገም የባንኮችም   የንብረት መብት እንዲሁ ይጣሳል፡፡

 

3.  ማጠቃለያ

በአጠቃላይ፣ አዋጁ ላይ ከተቀመጠው ሥርዐት ውጪ[11] ፍ/ቤቶች የባንኮች የመያዣ መብት እና አሻሻጥ ላይ ጣልቃ እንዲገቡና ሂደቱን እንዲያግዱ የሚደርግ ከሆነ፡-

·       በቀጥታ የአዋጁ አላማ እንዳይሳካ የሚያደርግና በውጤት ደረጃ  አዋጁን መሻር ስለሚሆን የባንኮች ህልውና እና የፋይናንስ ዘርፉ አደጋ ላይ ይወድቃል፣

·        በብድር የተሰጠው የህዝብ ገንዘብ በአግባቡ እንዳይሰበሰብ በማድረግ የብዙሃኑን አስቀማጭ መብት እንዲጣስ እና ዕድሜ ልክ በመስራት ያጠራቀሙትን ገንዘብ እንዲያጡ ይሆናል፣

·       በብድር የተሰጠው ገንዘብ በፍጥነት ለመሰብሰብ የማይቻልበት ሁኔታ ሰለሚፈጠር ባንኮች ብድር የሚሰጡት ረጀም ጊዜ ወስደው እና በከፍተኛ ወለድ ስለሚሆን የካፒታል እጥረት የሚፈጠር እና  የሀገርን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚስተጓጎል ይሆናል ፣

ባጠቃላይ የህዝብ ጥቅም(public interest)፣ ፈቃድ(consent) እና የሌሎች ግለሰቦችን መብት ማስጠበቅ(respect to others right) መሰረት አድረጎ የወጣ ህግ የግለሰቦች መብት ላይ  ተጽኖ ቢኖረው እንኳ ህገ-መንግስታዊ ቅቡልነት አለው፡፡አዋጅ ቁ 97/90 ከላይ የተገለጹትን ባህሪያት በሙሉ ያቀፈ ነው፡፡ ይሁንእንጂ፣ የፋይናንስ ዘርፉ የደም ሥር በመሆን ለህዝብ ጥቅም የመቆሙን ያህል የግለሰብ መብት ላይ አሎታዊ ተጽኖ እንዳይኖረው ተደርጎ የተቀረጸ ነው፡፡ ምክንያቱም 1ኛ)  የአዋጁ ተፈጻሚነት ስምምነታቸውን በሰጡ ግለሰቦች(በሌላ አነጋገር መብታቸውን በስምምነት በተው/"ዌቭ"ባደረጉ) ላይ ብቻ የተገደበ ነው፡፡2ኛ)እነዚህ ሰዎችም ቢሆኑ የአዋጁን ዐላማ በማይጥስ መልኩ  የመደመጥ እና በፍ/ቤት በኩል መፍትሄ የማግኘት መብታቸው ተረጋግጦላቸዋል፡፡

ይህ ሁሉ የመብት ጥበቃ አዋጁ ባካተተበት  ሁኔታ አዋጁን በመሸራረፍ  እና ለባንክ መያዣ የሰጡ ግለሰቦች የተለያየ ምክንያት ባመጡ ቁጥር ፍ/ቤት የሽያጩ ሂደት  ማንኛውም ደረጃ ላይም ቢሆን ጣልቃ ሊገባ ይቻላል የሚባል ከሆነ ግን ለአስያዡች ገደብ የለሽ መበት መስጠት ፣የገንዘብ አስቀማጮችን እና የባንኮችን የንብረት መብት ዋጋ ማሳጣት ይሆናል፡፡ ከላይ በተደጋጋሚ እንዳስቀመጥነው፣ከአዋጁ መንፈስ ውጪ የፍ/ቤት ጣልቃ ገብነት[12] የባንኮች ህልውና አደጋ ውስጥ ይጥላል፡፡ባንኮች ደግሞ ለሥርዐት ውድቀት አደጋ(systemic risk) የተጋለጡ በመሆናቸው ፣ ባንኮች አደጋ ውስጥ ሲገቡ አጠቃላይ  ኢኮኖሚው አደጋ ውስጥ ይገባል፡፡

------------//----------------



[1] የዚህ አዋጅ ይፋዊ መጠሪያ "በባንክ በመያዣ ስለተያዘ ንብረት የወጣ አዋጅ ቁጥር 97/1990" ነው፡፡አዋጁ በአዋጅ ቁ.216/192 እና አዋጅ ቁ. 1147/2011 ማሻሻያ ተደርጎበታል፡፡

[2] አዋጅ ቁ.97/90 አንቀጽ 3 (የ30 ቀን  ቅድመ ማስጠንቀቂያ መሰጠት እንዳለበት ይደነግጋል) እና አንቀጽ 6ን ይመለከቷል

[3] አዋጅ ቁ 97/90 አንቀጽ 3ን ይመልከቱ

[4] The waiver question also continued to arise in contexts not involving criminal procedure. In D. H. Overmyer Co. v. Frick Company (1972) and Swarb v. Lennox (1972) the Court reconfirmed earlier holdings that at least some civil litigants may contractually waive due process rights to notice and hearing prior to a judgment and thereby effectively waive the opportunity to contest the validity of a debt.    

[5] Simona Grossi, The Waiver of Constitutional Rights, 60 Hous. L. Rev. 1021 (2023).

[6] የኢትዮጽያ ብሔራዊ ባንክ በ2020 ባወጣው የFinancial Consumers Protection Directive 02/2020 ማንኛውም በብድር ውል፣በመያዣ ውልና ከነዚህ ውሎች ጋር በተያያዘ ቅሬታ ያለው ተጠቃሚ በአፋጣኝ አስተዳደራዊ ምላሽ እንዲያገኝ ሚያስችል አስገዳጅ መመሪያ አውጥቶ በስራ ላይ ይገኛል።በመሆኑም ባንኮች ለደንበኞቻቸው ቅሬታ በ10 ቀን ውስጥ ምላሽ  የሚሰጥ የቅሬታ ሰሚ ክፍል ማቋቋም አለባቸው።ተበዳሪው ወይም አስያዡ የባንኩ ቅሬታ ሰሚ አካል በሰጠው ውሳኔ ካልተስማማ ቅሬታውን ለተቆጣጣሪው ለብሔራዊ ባንክ አቅርቦ ከአስር ቀን በታች ምላሽ ያገኛል፡፡

 

[7] አዋጅ ቁ፣97/90 አንቀጽ 6 መሰረት የፍ/ሥ/ሥ/ህ/ 444-447 ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡

[8] አዋጅ ቁ፣97/90 አንቀጽ 7 ን ይመልከቱ

[9] በዚህ ጉዳይ ላይ ሁለት የአሜሪካ ፍ/ቤቶች ውሳኔ እንመልከት 1ኛ) Phillips v. Comm’r, 283 U.S. 589, 596–97 (1931) (“Where only property rights are involved, mere postponement of the judicial enquiry is not a denial of due process, if the opportunity given for ultimate judicial determination of liability is adequate.”). 2ኛ) Garcia, et al. v. Fed. Nat’l Mortgage Ass’n., et al (In the foreclosure context, these principles do not require a preforeclosure judicial hearing because the mortgagor is given timely and adequate notice of the reasons for the default in advance of the foreclosure and an pportunity to cure any default, …, as well as an opportunity to stop the foreclosure and set aside any resulting sale for “fraud or irregularity” in the process.)

[10] ከአዋጁ የምንረዳው ፍ/ቤቶች  ጣልቃ መግባት ያለባቸው የአዋጁ አንቀጽ 7ን መሰረት በማድረግ ወይም/ እና ከአዋጁ አንቀጽ 6 እንደምንረዳው የፍ/ሥ/ሥ/ህ/ 444-447 መሰረት በማድረግ ብቻ ነው፡፡

[11] ዝኒከማሁ  

 

[12] ከአዋጁ የምንረዳው ፍ/ቤቶች  ጣልቃ መግባት ያለባቸው የአዋጁ አንቀጽ 7ን መሰረት በማድረግ ወይም/ እና ከአዋጁ አንቀጽ 6 እንደምንረዳው የፍ/ሥ/ሥ/ህ/ 444-447 መሰረት በማድረግ ብቻ ነው፡፡

Share - The Constitutionality of Proc.97/98

Follow Guest to stay updated on their latest posts!

Follow

0 comments

Be the first to comment!

This post is waiting for your feedback.
Share your thoughts and join the conversation.